አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ – ጥቅምት 21/2012 ዓ.ም – በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወጣቶች አመርቂ እና አስተማማኝ የስራ እድሎችን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ለወጣቶች የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርገው ማስተርካርድ ፋውንዴሽን እና የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ኮሚሽን በጋራ በመሆን አዲስ በሚጀምሩት “ወጣቷ አፍሪካ በኢትዮጵያ ትሰራለች/ያንግ አፍሪካ ዎርክስ” የሚል ፕሮጀክት አማካኝነት ነው፡፡ ማስተርካርድ ለፕሮጀክቱ መሳካት የሚያግዝ የመጀመሪያ ዙር የ300 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡንም አስታውቋል፡፡

‘ያንግ አፍሪካ ዎርክስ’ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ካቀዳቸው አዳዲስ የስራ ዕድል መፍጠሪያ እቅዶች ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከትምህርት ተቋማት እና ወጣቶች ጋር በመተባበር የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው፡፡

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ከስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በቱሪዝም ፣ በግብርና ፣ በአምራች ኢንደስትሪ እና አይ.ሲ.ቲ. ዘርፎች ላይ እድገት በሚያመጡ ፕሮግራሞች ላይ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ፕሮግራሞቹም የስራ ፈጣሪዎችን እና የአነስተኛ እና መካከለኛ ቢዝነስ ባለቤቶችን የበለጠ አምራች እና ትርፋማ የሚሆኑባቸውን መንገዶች እንዲጠቀሙ የሚያግዙ ይሆናሉ፡፡

የስራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ “ኢትዮጵያ ልትበለፅግ የምትችለው ሁላችንም በየግላችን የአቅማችንን ስንሰራ ነው፡፡ ለሁሉም ዜጋ በተለይ ደግሞ ለወጣቶች እና ሴቶች ስራ መፍጠር ለህብረተሰባችን ተስፋ፣ ክብር እና የተሻለ ነገን እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው” ይላሉ፡፡

ፋውንዴሽኑ የመጀመሪያውን ዙር የፕሮጀክት ትግበራ አጋሮቹን ያሳወቀ ሲሆን እነሱም ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ኢንሴክት ፊዚኦሎጂ እና ኢኮሎጂ፣ ክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ፣ ፈርስት ኮንሰልት ፒ.ኤል.ሲ.፣ ዲ.ኤ.አይ. ዩሮፕ እና ኤስ.ኤን.ቪ. ናቸው፡፡

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለመፍጠር ከታቀደው 10 ሚሊዮን የስራ እድል ፈጠራ የመጀመሪያውን 1.4 ሚሊዮን የስራ እድል የሚፈጥረውን ፕሮጀክት ለማስጀመር 119ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሪታ ሮይ ሲናገሩ “በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ባደረኳቸው የተለያዩ ጉዞዎች ያየኋቸው ልዩ ልዩ የወጣቶች የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴዎች እና በማህበረሰቡ ላይ ያመጡት ትርጉም ያለው ለውጥ በጣም አስደስቶኛል፡፡ ‘ያንግ አፍሪካ ዎርክስ’ ፕሮጀክትም ለእነዚህ ወጣቶች የገንዘብ አቅርቦት፣ የቢዝነስ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ለሌሎች ኢትዮጵያውኖችም ተጨማሪ የስራ እድሎችን እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን ድጋፍ በማቅረብ እናግዛቸዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

ባለፉት አስር አመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ ውስጥ በ34 ሀገራት ሲሰራ የቆየው ፋውንዴሽኑ በተለይም በአስሩ ሀገራት ያለውን ቁርኝት ይበልጥ አጥብቆ እንደሚሰራበት አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በመንግሰት በኩል በታየው የተሸሻለ የግሉ ዘርፍ ልማት ቁጥጥር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመንትን ለማበረታት በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ስራ እና ቁርጠኝነት አማካኝነት ቅድሚያው ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ነች፡፡ እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮም ለፋይናንስ፣ ትምህርት እና የወጣቶች ህይወት ላይ የሚወል የ62 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ሰማሃል ጉዕሽ ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ስራ የጀመረው እና ከ80 ሰራተኞች ውስጥ 80 በመቶ ወጣት ሴቶችን ቀጥሮ የሚያሰራው የቀበና ሌዘር ድርጅት መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ነች። የ29 አመቷ የስራ ፈጣሪ የስራ ፈጠራና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ ስታስረዳ፣ “አባቴ ገና ልጅ እያለሁ መሆን የምፈልገውን ሁሉ መሆን እንደምችል ይነግረኝ ነበር፡፡ እኔም ያለማቋረጥ የተለያዩ የቢዝንሰ ሃሳቦችን አፈልቅ ነበር፤ ነገር ግን የራስን ቢዝነስ መጀመር ቀላል አልነበረም፤ ቢያንስ ለሁለት ጊዜያት ሳይሳካልኝ ቀርቷል፡፡” በማለት አብራርታለች።

ሰማሃል ቀጥላም “ይህም ሆኖ ህልምህን ከተከተልክ በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣት ትችላለህ፡፡ ሁሌም የሚያበረታኝ ነገር ቢኖር የምሰራው ስራ ትርፍን አስቤ ሳይሆን ለሌሎች ለመኖር በቂ የሆነ ገቢ የሚያስገኝ የስራ እድል ለመፍጠር እና እነርሱም በተራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ስራ ፈጣሪነቴ ሁሌም ቢሆን የድርጅቴ ምርታማነት፣ ፈጠራ እና ቀጣይነት እንዲያድግ እፈለጋለሁ፡፡ ይህም ማለት ተጨማሪ ገንዘብ እና የመስሪያ ቦታ ማግኘት ማለት ነው፡፡” ስትል ተናግራለች።

ያጋሩት