የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በጋራ የጀመሩት የ5 ዓመት ፕሮጀክት ፈጠራን በማበረታታት፣ አካታችና አነቃቂነትን መሰረት በማድረግ ፖሊሲዎችን በማሻሻል በኢትዮጵያ የተጀመረውን የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

“ኢትዮጵያን ማስቻል” ፕሮጀክት ሲቀረጽ የአገሪቱን የ5 ዓመት የስራ ፈጠራ መሪ እቅድ ለማሳካት አስተዋዕጾ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ አገሪቱን የስራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት አመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው። እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት አመት የስራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቬስትመንትን በማመቻቸት በ 2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።

በዚህ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ለስራ ፈጠራ ምቹ ምህዳር መፍጠር ፣ አስፈላጊ የሰው ኃይል ካፒታልን ማዳበርና ማክሮ ፖሊሲዎች ስራ ፈጠራን እንዲያበረታቱ ማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራባቸዋል።

ኢትዮጵያን ማስቻል ለ50 ሺህ ሴቶችና ወጣቶች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የስራ ዕድል በማመቻቸት የመሪ እቅዱን አፈጻጸም ያግዛል። በተጨማሪም ለስራ ዕድል ፈጠራ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጡ ማክሮ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹና አፈጻጸማቸውም ቀልጣፋ እንዲሆን የአቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ፣ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ግንባታውን በማገዝ እንዲሁም ሃብት በማሰባሰብ ስራዎች ላይ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።

ኢትዮጵያን ማስቻል ትኩረት ላልተሰጣቸው የማህበረሰብ አካላት ማለትም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለሚሰሩት ስራ ክፍያ የማያገኙ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት ዓላማ ያደረገ ነው። ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ክህሎት ከማዳበር በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ እምቅ ኃይል ያላቸው ስራ ፈጣሪዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ያደርጋል።

“ኢትዮጵያን ማስቻል ስሙም እንደሚያመለክተው ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ነው። በተለይም ትኩረት ያልተደረገባቸው ነገር ግን ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ስራ እንዲኖራቸውና ገቢ እንዲያገኙም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማመቻቸት እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለድርጅቶችና ለግሉ ሴክተር እንቅፋቶችን ለማስወገድ ትኩረት ፈጠራ ትብብርና ልህቀትን በመጠቀም ለሴቶችና ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የተከበረ እና አስደሳች የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ይተጋል” በማለት ዶር ኤፍሬም ተክሌ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ገልጽዋል።

ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መሪነት ሲሆን የፌዴራልና የክልል መንግስታት ፣የኢንተርፕራይዝ ልማት አካላት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ነው።

“ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ 10 ሚሊዮን ወጣቶች የተከበሩና አስደሳች የስራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ወጣት አፍሪካ በስራ ላይ ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር ባለን ትብብር የኢትዮጵያ ወጣቶች እድገት እንዲያስመዘግቡና የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በጉልህ እንዲታይላቸው የሚያደርግ ነው” በማለት አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ገልጸዋል።

ያጋሩት