የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በ2011 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአገራችን ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉ ያሉበትን የፖሊሲ ማነቆዎች በመፍታትና ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት እየሠራ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር በኢኮኖሚው እምብዛም ያልተለመዱ አዳዲስ የሥራ ዘፎች እንዲስፋፉ እንዲሁም የሥራ ገበያውን የተመለከቱ መረጃዎች ባንድ ማዕከል እንዲተነትኑና እንዲደራጁ በማድረግ በኩል አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል። የአሥር ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ ፍኖተ ካርታ (Road Map) እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድም አዘጋጅቷል። በፍኖተ ካርታውና ስትራቴጂክ ዕቅዱ በመመራት እስከ 2017 ዓ.ም 14,000,000 (አሥራ አራት ሚሊዮን) እና እስከ 2022 ዓ.ም ደግሞ 20,000,000 (ሃያ ሚሊዮን) ዜጎች ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትወያይቶና ተመካክሮ ተገባብቷል፡፡

በዚህ መሠረት ከፍኖተ ካርታውና ከስትራቴጂክ ዕቅዱ የተቀዳ ዓመታዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተቋሙ ተልዕኮ መሳካት መሠረት የሆኑ ውጤቶችን አስመዝግቧል። በ2012 በጀት ዓመትም እንደ አገር ለ3,000,000 (ሦስት ሚሊዮን) ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ3.4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን 330,000 (ሦስት መቶ ሠላሳ ሺ) የሚሆኑ ሥራዎች ደግሞ በኮቪድ-19 ምክኒያት ከስመዋል።

ለ3.4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ሲፈጠር ከፌዴራል እስከ ክልል ብሎም ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው አመራር ድርሻ የላቀ ሚና የነበረው ሲሆን የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ለማጠናከር በየደረጃው የተፈጠሩ አደረጃጀቶች/ Plat forms/ አበርክቶ ደግሞ እጀግ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በመሆኑም ከ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸምና ከአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ በመነሣት በአመራሩና በፈጻሚው ቅንጅታዊ ርብርብ በ2013 በጀት ዓመት 3,000,000 (ሦስት ሚሊዮን) ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም የተፈጠሩ ሥራዎች እንዳይከስሙ ለማድረግ ወደ ትግባራ ተገብቷል።

ለዚህ ስኬት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሪ ኮሚቴውን በመሰብሰብ ለ3,000,000 (ሦስት ሚሊዮን) ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲቻል አመራሩና ፈጻሚው በትኩረት እንዲሠራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በበጀት ዓመቱ ከፌደራል እስከ ቀበሌ የተቀናጀ የዕቅድ የሪፖርት እና የግምገማ ሂደት ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ እንዲቻል ዕቅዱ በአገር አቅፍ ደረጃ በኮር ቴክኒካል ኮሚቴ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። በፌደራል ደረጃ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት፣ ለፌደራል እና ለክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት የጋራ መድረክ ቀርቦና ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ተደርጓል። በዚህ መሠረት ዕቅዱ ከፌዴራል እስከ ክልልና ታችኛው መዋቅር ድረስ የሥራ አጥነት ምጣኔንና የወጣቶችን ቁጥር እንዲሁም የኢኮኖሚውን ሥራ የማመንጨት አቅም መሠረት በማድረግ ተሸንሽኖ ወርዷዋል። በተጨማሪም በክልልና በከተማ አስተዳደር የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ም/ቤቶች ሥራውን በባለቤትነት ተረክበው እንዲመሩት በክቡር ኮሚሽነሩ በሚመራ ቡድን በስድስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር በመገኘት የግንዛቤ መፍጠሪያና የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በመሆኑም በአገር ደረጃ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ450,000 (አራት መቶ አምሳ ሺ) ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ302,887 (ሶሰት መቶ ሁለት ሺ ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት) ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ይህ አፈጻጸም ከሩብ ዓመቱ ዕቅድ አንጻር 67 % ሲሆን ለዓመቱ ከተያዘው 3,000,000 (ሦስት ሚሊዮን) ዕቅድ አንጻር ደግሞ 10 % ነዉ።

ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ውስጥ 72 % ቋሚ 28 % ደግሞ ጊዜያዊ (ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚቆዩ) ናቸው። የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ውስጥ 38 % ሴቶች ሲሆኑ ይህን ለማሻሻል በቀሪው ጊዜ በትኩረት ይሠራል።

የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም በ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 302,424 (ሦስት መቶ ሁለት ሺ አራት መቶ ሃያ አራት) ጋር ሲነጻጸር በ463 (ሰድስት መቶ ስልሳ ሦስት) ብልጫ አለዉ። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት፣ የሰዉ ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መስፋፋት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ የመዋቅራዊ ችግር አለመፈታት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበ በጀት በቂ አለመሆን እንዲሁም በአብዛኞቹ ክልሎች መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን የብድር በወቅቱ አለማቅረቡ የተገኘው ውጤቱ ከቅዱ ዝቅ እንዲል ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከፍተኛ አፈጻጸም (85 %) ያሳዩት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርና ኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ አማራ ክልል መካከለኛ አፈጻጸም (61%) ነበረው። ቤንሻነጉል ጉሙዝ ክልል 57 ከመቶ፣ ሶማሌ ክልል 55 ከመቶ፣ ጋንቤላ ክልል 49 ከመቶ፣ ደቡብ ክልል 26 ከመቶ፣ አፋር ክልል 25 ከመቶ፣ ሀረሪ ክልል 30 ከመቶ፣ ድሬ ዳዋ 22 ከመቶ በመፈጸም ዝቅተኛ ውጤት ያሰመዘገቡ ናቸው።

ሊፈጠሩ ለታቀዱት የ3,000,000 (ሦስት ሚሊዮን) የሥራ ዕድሎች እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ የሚያስችል 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ በዕቅድ ተይዞ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገው መግባባት በአጠቃላይ 373.27 ሚሊዮን ዶላር በአገር አቀፍ ደረጃ በማሰባሰብ የዕቅዱን 74% ማሳካት ተችሏል። በተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ለማበራከት የሚያስችሉ Crowd Funding/Angel business/ የመንግሥት የብድር ዋስትና ሥርዓት ዝርጋታ የጽንሰ ሐሳብ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል።

በሩብ ዓመቱ በርካታ ማነቆዎች ያጋጠሙ ቢሆንም ዋነኛውና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ነው። ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በ2012 የተጠናው ጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው ችግሩ በዚህ ሁኔታ ቢቀጥል በርካታ ዜጎች ከሥራቸው ይፈናቀላሉ፤ አዳዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞች እስከመዝጋት የሚያደርስ ኪሳራ ይደርስባችዋል፤ በርካታ ሥራዎችም ይከስማሉ። ይህን ጥናት መሠረት በማድረግ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች ከማስተር-ካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የ24.8 ሚሊዮን ዶላር ችግሩ በሰፋበት አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። እስካሁን ባለው ሂደት ሥራውን እንዲያከናውን በተመረጠው ድርጅት የኦንላይን መተግበሪያ ተዘጋጅቶ ተጠቃሚዎችን የመመዝገብ ሥራ ተጀምሯል። በዚህ ድጋፍ 24,000 (ሃያ አራት ሺ) ኢንተርፕራይዞች የሚጠቀሙ ሲሆን በ50,000 (አምሳ ሺ) ተቀጣሪዎች ደግሞ ከሥራቸው እንዳይሰናበቱ ይደርጋል። መሰል ደጋፉ በሌሎቹ ክልሎችም ይካሄዳል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ የዝግጅት ሥራዎች በሚቀጥሉት ወራት ለምናካሂዳቸዉ ሥራዎች መሠረት የጣሉ ናቸው። በመሆኑም በዝግጅት ምእራፍ የተፈጠሩ መደላድሎችን በመጠቀም የኮቪድ ተጽእኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲጠናከሩ፣ የመረጃ ጥራት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የመረጃ ስርዓት ግንባታዎች እንዲቀላጠፉ፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂን ማእከል ያደርጉ አዳዲስ የስራ ዘርፎች እንዲበራበቱ፣ በጀትና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራዎች እንዲሰፉ፣ እንደዚሁም በየደረጃዉ የሚገኙ የሥራ እድል መዋቅሮች ቅንጅትና ትብብር እንዲጠናከሩ በትኩረት ይሠራል። በሂደቱ የሚለዩ ተግዳሮቶች እንዲፈቱም ርብርብ ይደረጋል።

ያጋሩት